ቅዳሜ 21 ኦክቶበር 2017

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ተፈጥሮ ታሪክ ማህበር በጋራ የአለም አቀፍ የስደተኛ አእዋፍ ቀን በሻላ፣ ጭቱ እና ዝዋይ ሀይቅ ዙሪያ በመገኘት ሀይቆቹ ላይ በተጋረጠባቸው ከፍተኛ አደጋ ላይና መፍትሄዎቹ ምንድን ናቸው በሚል ዙሪያ ውይይት በማድረግ አከበሩ፡፡

ከታዩት ችግሮች መካከል፤ የሀይቆቹ ውሃ መቀነስና ብክለት እየተባባሰ መሄድን ተከትሎ እየተከሰተ ያለው ተጓዳኝ ችግር ዋነኛው ነበር፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ዊት ላንድስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ፣ ብዝሀ-ህይወት ኢንስትቲዩት፣ ደንና አካባቢ ጥበቃ ሚንስቴር፣ ኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳትና ደን ኢንተርፕራይዝ እና የዘርፉ ተመራማሪዎች ተገኝተዋል፤ ውይይቱም ላይ ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
የዝዋይ ሃይቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውሀ መጠኑ መቀነሱ በዙሪያው ውሀውን የሚጠቀሙ ድርጅቶችና ግለሰቦች አግባብነት በጎደለው መልኩ መጠቀማቸው ምክንያት ሆኗል፡፡
ከዚህ ሀይቅም በመነሳት ወደ ሻላ ሀይቅ በመሄድ ይገብር የነበረው ቡልቡላ ወንዝ ሙሉ በሙሉ ጉዞው ተገትቶ ቆሟል፤ ስለሆነም በአቢጃታ ላይ የተከሰተው ከፍተኛ ችግር በሻላም ላይ በቅርቡ እንደሚከሰት አመላካች ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡
በቅርቡም በሻላ ሀይቅ ላይ ሊገነባ የታሰበው የሶዳ አሽ ፋብሪካ በርጋታ ሊጤን የሚገባው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ለእነዚህና ሌሎች ችግሮች ባለሙያዎቹ በመፍትሄነት ያቀረቧቸው ሀሳቦች የውሀ አጠቃቀሙ ሁለቱንም በማይጎዳ መልኩ እንዲሄድ በጋራ ስራዎችን መስራት፣ ውሀውን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሙ ድርጅቶች ተገቢውን ክፍያ በመክፈል እንዲጠቀሙና ይህም ሀይቆቹን ለመጠበቅ ለሚሰሩ ስራዎች አጋዥ እንዲሆን ማስቻል ፣የሀይቆቹን ዙሪያ ከበካይ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች መጠበቅ እና ጠብቆ በማልማት ይዞታቸው እንዲመለስ መስራት ሲሆን ይህ ሳይሆን አሁን እየተካሄደ ባለው መልኩ ያልተገባ አጠቃቀም ከቀጠለ ሀይቆቹ በቅርቡ ላለመጥፋታቸው ምንም ዋስትና እንደማይኖር የሚሉት የውይይቱ ሀሳቦች ነበሩ፡፡
ግንቦት 14/2009 /የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን / by anjel miro

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ